ሎንቺና

ሎንቺና: ከበቀለ ገብርኤል (ሲሳይ) ሚኒሶታ ---- Copyright@2004-2005, Bekele Gebriel

Source: http://www.selamta.net

ስውዬው ዘመዶቹ ወደ አሉበት ከተማ ለመሄድ ወደ አውቶቢስ መናሃሪያው ጎራ ይላል።

ትኬቱን ቆርጦ ወደ ውስጥ ገባ ሲል መጨረሻ ካለው መቀመጫ በስተቀር ሁሉም ወንበር ተይዞ ያገኛል። ወደፊት ሲመለከት የሹፌሩ ቦታ አልተያዘም እዚያ ኸላ ሄጄ ከምጋፋ ለምን እዚህ አልቀመጥም ብሎ የሹፌሩ ቦታ ላይ ቁጭ ማለት፡ ሹፌር ገባ ሲል ወንበሩ ቴይዞዋል በመገረም! “ምን እየሰራህ ነው የኔ ወንድም ይለዋል?” መንገደኛውም እያየኽኝ ምን ተጠይቀኛለሁ ተቀምጫለሗ ይለዋል፡ ሸፌሩም የሚያሾፍ መሰሎት በንዴት አንተ እሱ ጋር ከተቀመጥክ መኪናውን እንዴት ልናዳው ነው?” መንገደኛውም እዚህ ወንበር ላይ እንቁላል ጥላሃል እንዴ! ለምን ሌላ ወንበር ላይ ቁጭ ብለህ አትነዳም ብሎት እርፍ።

ለመግቢያ እንዲሆነኝ ብዬ ይህን ቀልድ ያመጣሁት ጽሁፌ ከሚያተኩርባቸው አንዱና ዋናው ክፍል የሎንቺናዬ ትዝታ ሴሆን በተጨማሪ ደግሞ ከቤተሰብ ጋር ወደ ሀገር ቤት ስሄድ በመንገድ ላይ ያየሁትን ገጠመኜን ለማውጋት ፈልጌ ነው፡ ጽሁፉ በተጨማሪ ቀልድ አዘል ምክሮችን ያካተተ ስለሆነ እያዝናና ብዙም ባይሆን መጠነኛ ትምህርትና ግንዛቤ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፡ ታዲያ በሃሳብ በአየር ላይ ከዋሸንግተን ዳላስ ኤይሮፕላን ማረፊያ አስከ ቦሌ አለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ትዝታዬንና ገጠመኜን እየኮመከማችሁ ቆይታችሁ ከኔ ጋር እንዲሆን እጋብዛለሁ።

የገዛነው የአየር መንገድ ትኬት የመቀመጫ ቁጥር ስላለውና ልጃችንም አብሮ ሰለነበር ግርግሩንና ግፊያውን ፈርተን ወደ መጨረሻው ላይ ነው አይሮፕላን ውሰጥ የገባነው። መግቢያው በር ላይ ስንደርስ ከእቅፍ አበባ በስተቀር የቀረ ነገር የለም፡ በሀገር ልብስና በአየር መንገዱ ዩኒፎርም ተውበው መንገዶኞቻቸውን እንኳን ደህና መጣችሁ ትኬቱን መልከት አድርገው እርሶ በዚህ በኩል ይሂዱ፡ የእርሶዎ መቀመጫ ደግሞ እዚያ ጋር ነው ብቻ ትህትናው ለረጅም ጊዜ ሰምቼው የማላውቀው አንቱ መባሉ እያስገረመኝና ውስጥ ውስጡን እያስደሰተኝ ወደ መቀመጫችን አመራን። ለምን እንደሆን አላውቅም ብቻ አብራሪዎቹና የሥራ ባልደረቦቻቸው የሀገሬ ልጆች ስለሆኑ ነው መሰል በቃላት ልገልጠው የማልችልው ኩራትና ደሰታ ተሰማኝ፡ በተለይ ቅድም ወደ ውሰጥ ከመግባቴ በፊት በርቀት ነጭ በነጩን ግጥም አድርጎ፤ በላዩ ለይ አረንጉዴ ብጫ ቀዩን ደርቦና አጃቢዎቹ መሀል የቆመ ሙሽራ መሰሎ Iትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላንን ሳየው እንባ ነው የተናነቀኝ። ቦታችን ከመግቢያው በር ብዙም ስለማይርቅ ቀድሞ በገባ ነው መሰለኝ ተይዞ አገኘነው፤ በሆስተስዎ ዳኝነት መቀመጫው ለኛ ከተፈረደልን በሃላ በእጅ የያዝናቸውን ትናንሽ ሻንጣ ለመክተት በዬ ከላይ ያለውን ማስቀመጫ ስከፍተው ጢቅ ብሎዋል፡ የሚቀጥለውን ሞከርኩ እስከ አፍጢሙ ድረስ ሞልቶዋል፡ በግራ በቀኝ ያሉትን እየከፈትኩ እየዘጋሁ ወደ መሀል ገሰገስኩ እድሌ ሆኖ ነው መሰለኝ ምንም በቅርብ ቦታ ማግኘት አልቻልኩም። አንዳንዱማ ለምን ከፈትኩት ነው የሚያሰኘው ቀድሞውኑ እንዴትሊዘጋ እንደቻለ ግራ ነው የሚያጋባው፡ ተዘጋ እንዴት ተደርጎ ጭራሽ አስተካክለው ያውም የሰውን ሻንጣ እንደምንም ብለው ዘግተው ይሄዳሉ፡ ለሚመለከት ሰው መቼም አይሮፕላን ውስጥ የእቃ ፍተሽ የተጀመረ ነው የሚመስለው። የሞት ሞቴን አንድ ክፍት ቦታ አግቼ ሻንጣዎቹን ወርውሬ ወደ ቦታዬ ተመለስኩ፡ በጣም ግርም ብሎኝ አሁን የኔ ቢጤ መንገደኛ በድንገት ቢታመምና መድሃኒት የምወስደው አለኝ ከሻንጣዬ ውስጥ አቀብሉኝ ቢል ሻንጣውን ፍለጋ ከዬት ነው የሚጀመረው? እንዳትስ ተፈልጎ ለገኝ ነው? ሰውዬው እንኳንስ ለመንቀሳቀስ የሚናገሩት በግድ ቢሆን እንዴት ሊኮን ነው? ሰውዬው በመድሃኒት እጦት ሳይሆን በመድሃኒት ፍለጋ ብቻ ህይወታቸው አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚደርስ አይመሰላችሁም? ደግሞስ ከህፃናት ጋር የሚጋዙ መንገደኞች አሉ ከሽንት መቀየሪያ አንስቶ እሰከ ትኩሳት መድሃኒት፤ ከመጫወቻ እስከሚንበቡ መፅሃፍቶች እዚሁ በእጅ የሚያዙ ሻንጣዎች ውስጥ ነው ያሉት ህጻኑ ባለቀሰ ቁጥር ሻንጣ ፍለጋ ሊኬድ ነው? የኔ ቢጤ ቀልበቢሱ ድግሞ ቦታ መገኘቱን እንጂ አቃውን ያሰቀመጠበትን ቁጥር ያልያዘ ወይም ምልክት ያላረገ ይኖራል ህጻናት ያላቸውን ወላጅ ጠጋ እያሉ ሻንጣዬን ያስቀመጥኩበት ስለጠፋኝ እንዲህ ያለ ነገር አበድሩኝ ሊባል ነው ደግሞስ ምልክት ላድርግ ቢባል እንዴት የቻላል! መንገድኛው በሙሉ ከጥቂቱ በስተቀር የሀገር ልጅ ነው መልኩ ይመሳሰላል፡ አትሳቁብኝና ሁላችንም ወደ ሐገር ቤት ስንሄድ ትብዛም ትነስም ቋጥረናት የምንሄደው ገንዘብ አለ ሚስጥር አወጣህ ስለምትሉኝ የሄኛው ምሳሌ እንኳን የቅር ለማለት የፈለኩት ግን ሳይገባችሁ አይቀርም፡ ባአጭሩ ለማለት የፈለኩት ምን አለበት እነዚህ በእጃችን የምንይዛቸውን ትናንሸ ሻንጣዎች በመቀመጫችን ትይዩ ባለው ማሰቀመጫ ውሰጥ ብናስቀምጥ።

እንዲሁ ከራሴ ገር ስሟገት የአይሮፕላን መነሻ ደርሶ ጉዟችንን ጀመርን፡ ብዙም አልቆየንም የራት ሰአት ደርሶ ከበላን በሃላ ድካሙም የእንቅልፍ ሰኣትም ስለሆነ ነው መሰለኝ ግማሹ ሲተኛ ሌላው እግሩን ለማፍታታት እያለ ከመቀመጫው ተነስቶ ወዲያ ወዲህ ይላል፡ ባለቤቴና ለጄም ለፓለይቶቹና ለራሳቸው የጸለዩ ነው የሚመስለው አተኛኘታቸውን ላየ! አየር ላይ ያሉም አይመስልም።

እኔ ፊልም የተባለውንም ለማየት አልፈቀድኩም ብቻ በሃሳብ ጭልጥ ብዬ በህይወት የሌለውን፤ ቤተሰብ፤ ጎረቤት፤ ጓደኛ፤ ድሮ ሰፈር ውስጥ ተሰብስበን የምናባርረውን ውሻ፤ ውሻው ለምን ተነካ ብሎ በተራው የሚያባርረንን እብድ፤ ዳገት ላይ ደክሟቸው በሩጫ ደርሰንባቸው ከሗላ እንደ ብስክሌት የምንፈናጠጣቸው ከባድ የጭነት መኪናዎች፤ ደብተራችንን መሬት ለይ ቁጭ አድርገን በአካባቢው የሚሠሩትን ሹፌሮች ወደ ትምህረት ቤት እንዲወሰዱን የምንለምነው ልመና፤ መኪናው ሲቆም ሁላችንም አንድ ላይ መግባት ያለብን ይመስል በሩ ላይ የምናደርገው ትንንቅንቅ፤ የአውታንቲው (ረዳቱ) ካልቾ፤ ስንቅ አመላላሻችን ሎንቺና ተበላሽታ ከቀረች ለባለንብረቱ ሳይሆን ጾም በማደራችን የምናዝነው ማዘን አረ ምኑ ቅጡ ትዝታዬን ወደሃላ እያጠነጠንኩ አስነካው ጀመር።

አልፎ አልፎ በዚያ ትህትና በተሞላው አነጋገራቸው በና ይፈልጋሉ? የሚጠጣስ?” እርስዎ ተብዬ እንዴት እምቢ አላለሁ እያልኩ ቡናውን በላይ በላዩ ሰለው እንቅልፍ ለምን ድራሹ አይጠፋም መሰላቸሁ ተመልሼ ወደ ትዝታዬ።

በተለይ በጉዞ ለይ ስላለሁ ነው መሰለኝ ከወረዳ ወረዳ፤ ከወረዳ አውራጃ፤ ከወረዳ ዋና ከተማ የምመላለስባቸው መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች ትዝ አሉኝ፡ እንደሚጭኑት የሰው ልክ የተለያየ መጠሪያ አላቸው፡ ሎንቺና፤ ቺኳንታ፤ ጠልፎ ሌላም ተብለው ይጠራሉ። በተለይ ለሎንቺና ትልቅ ቦታ እሰጣታለሁ በልጅነቴ አቧሯዎን እያቦነነችብኝ ከሃላዎ የሚወጣውን ጪስ እያጠነቺኝ ከትምህርት ቤት ወደ ትምህርት ቤት እያመላለሰችኝ ስላደኩ ነው መሰለኝ የዛሬውን የትዝታዬን ትልቁን ሥፍራ ይዛለች ለማስታወሻም እንዲሆን ብዬ የፅሁፌን አርእስት በሷ ስም ሎንቺና ብዬ ሰይሜዎለሁ።

ሎንቺናን ለማታውቁ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ስትሆን ወደ ሀያ አምስት ሰው እንድትጭን የተፈቀደላት ነች ታዲያ ይሄ በህግ የተፈቀደላት ሲሆን እንደ እድሜዎ ክብደቶና ጤንነቶዎ ታይቶ ደግሞ ቁጥሩ ከፍ የሚልበት ጊዜ አለ። ከመንገዶኞቻዎ ቋሚ ደንበኞች አንዱ ተማሪዎች ስለሆን ህገ ወጥ ድርጊትም እንድታደርግ የገፋፋን የመስላል፡ አንዳንዴ በሥነ ሠርአት ከመነኸሪያዎ ሙሉ ሰው ጭና በመጓዝ ያለችው ሎንቺና ሌላ ተሣፋሪ በገኘች ቁጥር ማስገባት ትጀምራለቸች፡ አውታንቲውም ተሜ ጠጋ በልላቸው እዚህ ቅርብ ነው የሚወርዱት ይላል፡ ሌሎች ደግሞ እንደዚሁ በእጃችው ምናምን የዘው የሚገቡትን ተሜ ዶሯቸውን እግርህ ሥር አድርግላቸው እንቁላሉ ደግሞ እንዳይሰበር ከደብተርህ ገር የዘው እድሜ ደግሞ ጠና ያሉት ወይም ህመምተኛ የሚመስሉት ሲገቡ ተነሱላቸው ወይም ተደራርባችሁ ተቀመጡ እኛ መታዘዝ ነው ምክንያቱም ሁሌም ባይሆን አልፎ አልፎ ሳንከፍል በነፃ ነው የምንሄደው፡ ብቻ ሁለት ሰው ማስቀመጥ አለበት የተባለው መቀመጫ ብዙም ኪሎ ስለሌለን ነው መሰል አራት ወይም አምስት ሆነን እንሞላዎለን። ግን ትልቁ ችግር ትራፊክ ወይም ተቆጣጣሪ የመጣ እለት ነው።

ተቆጣጣሪን ሳስታውስ አሁን ድረስ በጣም የስቀኛል ለማን እንደሚሠራ የሚያስገባው ገቢ የት እንደሚሄድ በትክክል የማውቅ አይመሰለኝም፡ እንደ አየሩ ፀባይ ሲፈልገው ኮት ብርድም ከሆነ ነጠላ ሲሻው ባርኔጣ ካልሆነም ከዘራ ብቻ ከሩቁ ሲታይ ከሌላው ሰው በምንም አይለይም የሹፌሮች ጌታ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡ ምልክት ነገር በእጁ ላይ ስለሚይዝ ማንኛውንም የህዝብ ማመላለሻ የሚነዳውን ሹፌር የትም ቦታ በማንኛውም ሰአት ማስቆም የችላል፡ ከፈለገ ውስጥ ገብቶ ትርፍ የተጫነ ሰው ካለ ካርኒ ቆርጣ መስጠት ይችላል፡ የሥራውም ፀባዩ ስለሆነ በነጻ መጓጓዝ ይችላል።

የሎንቺናም ሆነ ሌሎች የህዝብ ማመላለሻ ሹፌሮች ለነዚህ ዩኒፎርም ለሌለቸው ትራፊኮች የተለያየ የቅፅል ስም ሰጥተዎቸዎል። ከህጉ ወለም ዘለም የማይለውንና መንገደኞ ተጉላሉ አልተጉላሉ በዙም ግድ የማየሰጠውንና ሲሻው መንገደኛውን እያሰወጣ የሚቆጥረውንና ትርፍ በጫነው ልክ ካርኒ የሚቆርጠውንና የሚያስቀጣውን ገገማ ይሉታል፡ ሌሎቹ ነብሰ በላዎቹን ደግሞ ጭልፊት ነው የሚሏቸው እነዚህ ጋር ቀልድ የለም መፈክራቸው ትርፍ የጋር ነው ጸጥ ባለ ጠራራ ፀሐይ ከየት መጣ ሳይባል ሎንቺናዎን ሲያስቆም ላየ ጉድ ነው የሚያሰኘው ሎንቺናው በምን ያህል ፍጥነት እንደሚሄድና ጎማው ተንሸራቶ የት ጋር እንደሚቆም ከሹፌሩ በላይ የሚያውቅ ነው የሚመስለው፡ ሹፌሮቹም እንደዚህ አይነቶቹን ስለሚያውቋቸው አውታንቲው (ለረዳቱ) መጀመሪያው ጠያቄቸው ስንት ሰው ትርፍ ጭነሀል?” ነው፡ ሹፌሩም ቶሎ ወረድ ብሎ እጅ ከነሳ በሁላ ወደ ሎንቺናው በስተጀርባ ይሄዳሉ፡ የት አባቱ! አገኘው ዘሬ በንዴት መቼም ሳይገለብጠን አይቀርም ስንል ጭራሽ እየሳቀ እያፏጨ ይመጣል፡ በራሱ ምርጫ ለሱ የሚስማማውን ቴፕ (ዘፈን) አስገብቶ እሱን እያዳመጥን ጓዟችንን እንቀጥላለን፡ የሚቀጥለው ከተማ ሹፌሮች ዜና የሚቀያየሩበት ሲሆን እንዴት ነው መንገዱ ሰላም ነው?” ተጠንንቀቅ ጭልፊቷዎ አለች ወይም ገገማው ተነስቶበታል እየተባባሉ መድረሻችን ደርሶ እንወርዳለን።

ታዲያ ይሄንን እያየን ወደ ፊት ስታድጉ ምን መሆን ትፈልጋላችሁ ብሎ ለሚጠይቀን ከዶክተር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ተቆጣጣሪ ብንል ሊገርማችሁ አይገባም ምክንያቱም ብትሉ እንደ ጭልፊት አይነቱ እህል ለመሸመትም ይሁን ለማስጫን ደሞዎዙን የሚጠቀም አይመስልም ሲርበውም ይሁን ሲጠማው ሹፌሮች ቡናቤት ጎራ ማለት ነው ያዘዘው ምግብ ሳይመጣ ሂሳብ ተከፍሎ ይጠብቀዋል ታዲያ ኮሌጅ ብንበጥስስ ከዚህ በላይ መኖር እንችላለን።

እንዲያው ግማሹ መንገደኛ ወጥቶ በግፊ የሚያስነሳትን ሎንቺናህን ብዙ ካብካት አትበሉኝን መንገደኞቿዎን እንዴት እያዝናናች እንደምትጓጓዝ ውስጡን ላየ መፍረድ ይችላል። የዛሬውችን አላውቅም እንጂ የኔዎን የጥንቷን ሎንቺና ከውጪ ላያት የተጎሳቀለች ብትመስልም ወደ ውስጥ ገባ ሲባል አዝናኝ የሆኑ ስእሎቿና ማስጠንቀቂያዋቿ በየቦታው ተሰለውና ተለጥፈው ይገኛሉ Iሊዎቹም ሆኑ ማስጠንቀቂያውን የፀፉት መንገደኛው እንዳይሰለቸው እየሳቁ እየተነጋገሩ እንድሄድ ሆን ብለው ያደረጉት ነው የሚመስለው።

አንዳንዴ የተፀፈው ማስጠንቀቅያ በህግ የተከለከለ ነው መኪናው በመጓዝ ላይ እያለ ሹፌሩን ማነጋገር በህግ የተከለከለ ነው” “መኪናው እየሄደ መውረድ በህግ የተከለከለ ነው ሌላም ሌላም፡ ህጉን ተላልፈው ቢገኙ የትኛው ከተማ ወይም ፓሊስ ጣቢያ እንደሚቀጡ የታወቀ ነገር የለም ምክንያቱም ብዙ ከተማዎችን አቋራርጠው ስለሚሄዱ። ሌሎች ደግሞ ይህ የሚያመጣውን ችግር በመረዳትም ይሁን መንገደኞቻቸው በየፍርድ ቤቱ እንዳይጉላሉና አላስፈላጊ የሆነ ወጪ ለጠበቃ እንዳያወጡ አሻሸለው መኪናው እየሄደ ሹፌሩን ማነጋገር ለአደጋ ያጋልጣል” “መኪናው እየሄደ መውረድ ክልክል ነው” “መትፋት ያስነውራል ሌላም ሌላም በተለይ በልጅነት ጊዜዬ የነበሩትን ሎንችናዎች ያየ የስእሎቹ ትዝታ የሚጠፋ አይደለም አንዳንዴ ሀገሪቷ ውስጥ የሉት የዱር አራዊቶች ከሶስት የሚበልጡ አይመስሉም የሚሳለው አንበሳ፤ ነብር ወይም ሌላ አንድ አውሬ ነው፡ አንዳንዴ አንበሳ ሲሳል አጠገቡ ከተሳሉት ቤቶችም ይሁን ከጎኑ ከተሳለው ተራራ የትና የት ይበልጣል፡ አንበሳን በአይኑ ወይም በፎቶ ላላየ ወይም በወሬ ከሌላ ሰው ላልሰማ አንበሳና ከተራራ ማን ይበልጣል ቢሎት እንዴታ አንበሳ ነዋ! ቀጠል አድርገው ታዲያ ተራራ ሲወጣና ሲወርድ አንዴት ነው ቢሉት ይራመደዋል ቢልዎት ሊገርሞት አይገባም እርሶም የተሳለውን አንበሳውን ግዙፍነት አየዩ፡ ጎጆ ቤት ሲሳልማ አንዳንዴ የቤተሰብ የፎቶ ጊዜ የደረሰ ይመስላል ከዶሮ ጫጩት እስከ በሬ በዚያችው ሀነስተኛ ቦታ ላይ ተስሎ ያገኙታል አንዳንዴ ተሰብስበው ሣር የሚበሉም ይመስላል ደግሞ ውሻ ስላለበት ሣር መብላት ጀመረ አንዴ ይላሉ! ግርም የሎትና ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው እነዚህ ሁሉ የቤት እንሰሳ በአንድ ገበታ ቀርበው መብላት የጀመሩት የላሉ፡ ሁለት ኮረዳዎች እህል በሙቀጫ ሲወቅጡ ተስሎ ላየማ ጉድ ነው የሚያሰኘው የዘነዘናው አነሳስና ከፍታው ከላይ ሲመለስ ሙቀጫ ውስጥ ሳይሆን የሌላኛው መሐል አናት ላይ የሚያርፍ ነው የሚመስለው የሌላዋም አስተያየት አድርገሺው ነው እንዲያውም ኑሮ መሮኛል የምትል ነው የሚመስለው፡ ሁሌ አዳኝ እንደዛ ከሆነ አደንን ጊዜ ለማሳለፊያ ሳይሆን መተዳደሪያችን ነው በሎዎት ሊገርሞት አይገባም ምክንያቱም የሚሳለው አዳኙ በጦር ሲያባርርና ሲገድል ነው ያውም ነብርን የሚያክል ነገር፡ አንዳንዴማ አዳኙ እጅ ጦሩ እያለ አውሬው ደምቶ ያዩታል በዘህ ላይ በመሃላቸው ትልቅ ወንዝ አለ እንዴ!! ብለው እንቆቅልሹን ለመፍታት ሲሞክሩ መውረጃዎ ደርሶ ይወርዳሉ፡ ቀለሙማ እርጅና ምክንያት የለቀቀውን ሲያዩ አውሬው ውሀ ነው ሰማይ የሚጠጣው ይላሉ ሁሉም ቀለሙ አንድ አይነት ስለሆነ። ከሀሳቤ ብንን ብዬ ቀና ስል የማየው ምልክት ሲጋራ ማጨስ ክልክል ነው” “እባክዎትን የመቀመጫ ቀበቶዎን ይሰሩ ኤዲያ ብዬ አይሮፕላኑ በነዚያ ስእሎች ቢያሸበርቅ ጉዟችን ምን እንደሚመስል ታየኝ።

የመጀመሪያ መቆሚያችን ሮም ሰለነበር እዚያ አረፍን፡ መቼም በሩ ላይ የነበረውን ግርግር ለተመለከተ ጉድ ነው የሚያሰኘው በተለይ የተወሰኑ የሠፈር ልጆች ይመስላሉ የመግቢያውንና የመተላለፊየውን መንገድ ይዘው ወሬያቸውን ያደራሉ፡ መውረድ የነበረበትም ሆነ ሌላ የሚገባ መንገደኛ እባካችሁ አሳልፉን እያለ ልመና ሆነ፡ እግሩን ለማፍታታት ሆነ ወደ ሽንት ቤት ለመሄድ የሚፈልግ ትልቅ እንቅፏት ነው የሆኑት፡ አይሮፕላኑንም ለማፅዳት የገቡትም የሮም አየር መንገዱ ሠራተኞች ጣሊያንኛውም ባይገባኝም አጠያየቃቸው መተላለፊያውን መንገድ ዘጋችሁብን ልቀቁልን የሚሉ ነው የሚመስለኝ ብቻ ምን አለፋችሁ ትርምስምሱ የወጣ ነበር ሎንችናዬ ማሪኝ ነው የልኩት።

የሮም ቆይታችን ካበቃ በሗላ ጉዟችንን ጀመርን የቀረን ሰአት በቲቨው እስክሪን ላይ ስለሚታይ እንደ እርጉዝ ሰአት መቁጠር ሆነ፡ ቅድም ሮም ስናርፍ ያየነው ድራማ አሁን ወደ ቲያትርነት የተቀየረ ይመስላል ተዋንያኖቹ አብዛኛው የተወሰኑ ሰዎች ሲሆኑ አልፎ አልፎ ከማን አንሼ የመስላል ቋሚ ደንበኝነታቸውንም ለማሳየት ብቅ ጥልቅ የሚሉም አልጠፉም ከበው ብቻ ሥነ ሥርአት ባልያዘ መንገድ መተላለፊያው መንገድ ለይ በመቆም ማውራት መደማመጥ ያለ አይመስልም መቼም የመጀመሪያውን ረድፍ የዘው የተቀመጡ ሰዎች መንኛ ይናደዱ ቦታ አልበቃ ሲላቸው እነሱ ትከሻ ላይ ነው መቀመጥ የሚቀራቸው፡ የሉኝታ የሚባል ነገር አጠገባቸው ያለፈ አይመሰልም አንዳንዱማ ያዝኑለተል ስንትና ሰንት ሰአት ቆመው ሲያዩት ምነው ትንሽ አረፍ ቢል ይላሉ የተገላቢጦሽ መሆኑ ነው።

መንገዱ አያደክምም አያሰለችም አይባልም ግን ተራ በተራ ቢሆንና ሥነ ሥርአት ባለው መንገድ ቢሆን ጉዟችንም እንዴት ያማረ በሆነ ነበር።

እንዲሁ እያልን ወደ አዲስ አበባ እየቀረብን መጣን የአየር ላይ ጉዟችን አሳዛኙና አስቀያሚው ክፍል ከዚህ በሗላ ያለው ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡ አይሮፕላኑ እግሩ መሬት ሳይነካ ያውም ገና በሰአት የሚቆጠር ጊዜ እያለ አንዳንዱ እየተነሳ እነዛ በእጅ የሚያዙትን ሻንጣ ማውረድ መጎተት መተላለፊያው መንገድ ላይ መደርደር ሆነ አንዳንዱማ ሻንጣውን አቅፎ የተቀመጠውን ሲያዩ አይሮፕላኑ እስኪያርፍ የሚጠብቅም አይመስልም በፓራሹት ሊውርድ የተዘጋጀ ነው የሚመስለው፡ የሆስተሶቹን ፊት ላየና የሚሉትን ለሰማ በጣም ነው የሚያዝነው፡ እባካችሁ አይሮፕላኑ ገና አላረፈም የወረዳችሁትን እቃ መልሱ ማን ሰምቶ ቀጠል አድርገው ህጉን ሥነ ሥርሃቱን በድንገተኛ ማረፍ ቢገደድ የሚያመጣውን ችግር ማን ሰምቷቸው አንዳንዱ ወደ እግሩ መሀል ገፋ ሲያደርገው ሌላው እንደ ህጻን ልጅ ሻንጣውን በጭኑ ላይ ተሸክሞ ሲሄድ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ሲረዱ ነው መሰል የመቀመጫ ቀበቷቸውን አስረው ቁጭ። እግዚሐብሔር አይበለውና አይሮፕላኑ በችግር ምክንያት ማረፍ ተገዶ ቢያርፍ የሚያመጣውን ቀውስ መገመት አያዳግትም በመጀመሪያ ህይወቱ የሚተርፈው በመተላለፊያው ላይ የተደረደረው ሻንጣ ነው ምክንያቱም ለመርዳት የሚገባውም ሆነ መውጣት የሚፈልገው መተላለፊያው ላይ የተደረደሩትን ሻንጣዎች መንገድ ስለዘጉ እነሱን ካላስለቀቀ የሌላውንም ሆነ የራሱን ህይወት ማዳን አይችልም።

መቼም የሎንቺናዬን ገበናዎን እንዲህ ዘክዝኬ አውጥቼ ያላትን መልእክትም ሆነ አስተያየት ሳላስተላልፍ ብንለያይ እርግማኗም የሚደርስብኝ ነው የሚመስለኝ። Iትዮጵያ አየር መንገድ በጉዞ ላይ እያለን የሚሠጡን የሃሳብ መስጫ ላይ የሚከተለውን እንዳሰፍር ጠይቃኛለች። መቼም ጉዞን በተመለከተም ይሁን ሰውን አንድ ሥፍራ ወደ ሌላ በማጓጓዝ እኛ በምድር ላይ ያለነው የቀደምትነቱን ሥፍራ መያዛችን ታውቁታላችሁ ብዬ እገምታለሁ ደግሞ እድሜና ልምድ ብዙ ያስተምራልና ያለንን አሰተያየት ብንሰጥ ቅሬታ የሚሰማችሁ አይመስለንም ደግሞ ተግባራዊ እንደምታደርጉት እምነታችን ነው።

እድሉ ገጥሞን በአይናችን ባናይም የድሮ ደንበኞቻችን ከባህር ማዶ አልፎ አልፎ ሲመጡ አንዳንድ ቅሬታ እንዳላቸው ሲናገሩ ሰምተናል፡ ለምሳሌ መንገዱ ሩቅ ነው፤ ጉዞው አሰልቺ ነው፤ ምግቡ በሹካና በማንኪያ የሚበላ ነው፤ ብዙ የሚያዝናና ነገር የለም ወዘተ መቼም የኸንን ስንሰማ ጆሯችንን ማመን ነው ያቃተን፡ እንዴት ጊዜ ማሳለፊያ ይጠፋል! አጫጭር ድርሰቶች፤ ቀልዶች፤ ተረተትና ምሳሌው፤ እንቆቅልሹ ሌላም በፅሁፍ የተዘጋጁት የት ደረሱ? እንዳይጠፉ ከፈራችሁ ትኬት እንደ መያዣ እየያዛችሁ በውሰት መልክ መስጠት ይቻላል ደግሞስ ዳማው፤ ገበጣው፤ ሠንጠረዡ ለጊዜ ማሳለፊያ ያንሳሉ ብላችሁ ነው፡ ፊልሙስ ቢሆን ስንት የቱሪስት አይን የሚስቡ የታሪክ ቦታዎች፤ ብርቅዬ የዱር አራዊቶች አንቱ የተባሉ ሯጮዎች ሲሮጡ የተዘጋጀ ሞልቶዋል እነሱ መታየት አይችሉም? ደግሞ ይሄ በሹካ የሚበላ ምግብ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው! እንጀራ ጠፍቶ ነው? ለዚህ አንድ ድንኳን ለማይሞላ ሰው አሥር አገልግል ብትሠሩ ቀጥ አድርጎ ያን ሁሉ ሰው አይሸኝላችሁም ይበላሻል እንዳይባል ማቀዝቀዣ አለ ታዲያ ያንን ሞቅ እያደረጋችሁ ማቅረብ እንዴት ያቅታል? መንገደኛውስ እየተጎራረሰ በሄድ ምን አለበት? ደግሞ ሰርግ ወይም ድግስ ሲደገስ ያንን ሁሉ ሰው አንድ ማሲንቆ ወይም ክራር የያዘ ሰው እንዴት እንደሚያዝናና አይታችሃል ታዲያ አንድ ማሲንቆ ተጫዎች ወይም ክራር ደርዳሪ ቋሚ ሠራተኛ አድርጋችሁ ቀጥራችሁ መንገደኛውን እያዝናና እነሱም እየሸለሙት ቢጓዙ ችግሩ ምንድነው? እንግዲህ የሚመስለንን መክረናል ሰሚ ከጠፋ ግን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የአውራ ጎዳናም ሆነ የባቡር ሐዲድ መዘርጋቱ አይቀርም እናማ የቀማችሁንን መንገደኞች መልሰን እንወስዳለን የሚል እምነት አለን። በመጨረሻም ጽሑፌን ከመደምደሜ በፊት የግሌ የሆነውን አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ።

ከላይ ልጠቅሰው እንደሞከርኩት በተለይ በጥቂት ሰዎች ሥነ ምግባረ ብልሹነት ይሉኝታ ማጣትና ያለመተባበር አሰተናጋጆቻችንን ወይም ሆስተሶቹን ብናስኮርፍም ይኼ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ነው ብለው በይቅርታ እንደሚያልፉን አምናለሁ። መቼም ከባሕር ማዶ ያለ ሰው እረፍትም የሁን ለሌላ ጉዳይ ወደ Iትዮጵዩያ ሲኬድ አሁንም በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች በሚያሳዩት አጓጉል ፀባይ በጅምላ አንድ ላይ ሲወገዝና ሲኮነን ይሰማል። እዚያ እያለሁ ምን እንደሰማሁ ልንገራችሁ፡ ጓደኛዬ አሜሪካ የምትመጡት ምን እንደምትባሉ ታውቃለህ አለኝ? ጆሮ መቼም የማይሰማው ነገር የለም ንገረኝ አሰኪ ምንድነው የምንባለው አልኩት!? ዋት አፕ መጡ ነው የምትባሉት አለኝ፡ በጣም ገርሞኝ አራስ ልጅ እስከ አዛውንት ከውጪ ወደ ሀገር ቤት የሚሄድ አሉ ታዲያ እነዚያ ሁሉ ተጠቃለው በተባለው አባባል ሲጠሩ በጣም ነው የሚያሳዝነው ሌላው ይቅር ይታያችሁ አናቶችና አባቶች ለእረፍት ከዚህ የሚሄዱት ያንን አይነት ስም ሲያገኙ! ልሳሳት እችላለሁ ግን ስሙ የወጣው አሁንም ጥቂቶቹ በሚጠቀሙት ጉራማይሌ ቋንቋ በሚያሳዩት ኩራትና ንቀት ነው ብዬ እገምታለሁ።

በጣም የሚገርመው እንቅልፍ መተኛት አለቸልንም የቤተሰብ የሀገር ናፍቆት ሊገለን ነው ብለን እድሉን አግኝተን ስንሄድ ሻንጣችን ብቻ ከቤተሰብ ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፎ ሲመለስ እኛ እንዱሁ ስንብከነከን ቤተሰብም የሁን ዘመድ በድንብ አይቶ ሳይጠግበን የምንመለስበት ጊዜ አለ፡ ትንሸ ጊዜውንም አግኝተን ለመጫወት ምክረን ያሳደገን ቋንቋ ያውም በቅርብ ከሀገር ወጥተን የጠፋን የመስል አስተርጓሚም የምንፈልግም አንታጣም፡ በስንት ቅመም እብድ ብሎ በቤተሰብ የተሠራውን ምግብ እያናናቅንን አቃቂር እያወጣንለት እገሌ ምግብ ቤት ጥብስ ጣት ያስቆረጥማል እያልን ሆቴሉን ጭምር የምናስተዋውቅ ሞልተናል።

በዚያው መጠን ደግሞ ቤተሰብ የሚበሉትን በልተው፤ የሚጠጡት ጠጥተው፤ አልጋ ቢጠፋ መሬት ላይ ተንከባለው፤ የቀኑ አልበቃ ብሎ ለሊቱን ከቤተሰብ ጋር በጫወታ አንግተው፤ የታመመ አስታመው፤ የሞተ ቀብረው፤ ባጋጣሚ ሆኖ ያልቀበሩትንም ለቅሶ ደርሰው አጽናንተው፤ የመጡበትን ሀገር ህይወት በሚገባ አስረድተው፤ ገንዘቡም እንዴት ተለፍቶ እንደሚገኝ ነግረው፤ ትልቁንም እነደትልቅነቱ ትንሹንም እንደ ትንሽነቱ አክብረው ጎሽ ልጅ ከተወለደ አይቀር እንደዚህ ነው ተብለው ራሳቸውንም ቤተሰብንም አስመስግነው የእረፍት ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲለያዩ ልክ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሀገር እንደወጡት ተላቅሰው የሚለያዩ መልተዎል። እርግጥ ዋት አፕ ለተባለውም ቡድን ሲመለስ ወላጅ ማልቀሱ አይቀርም ነገር ግን ለቅሶው ለማሳደግ፤ ለማስተማር፤ ውጪ ለመላክ የደከሙት ምንም ሳየመስላቸው በልጄ ያልፍልኛል፤ ሳረጅ የጦረኛል ወይም ትጦረኛለች ያሉት እራሱንም ወይም እራሷን መርዳተቸው እያጠራጠራቸው ሌላ ሌላ ነገር ውስጥ ገብቶ ወይም ገብታ ተመልሰው ይመጡብን ይሆን እያሉ የስጋት ወይም የፍርአት ለቅሶ ነው ብዬ ነው የምገምተው።

ባጭሩ ከኑግ የተገኘ ሰሊጥ…..” አይነት እንዳይሆን ስንዴው እንክርዳዱ እየተለየ ቢወቀስ ወይም ቢመሰገን ተገቢ ነው እላለሁ። በገባሁት ቃል መሠረት አየር ላይ ጉዟችንም አልቆ አይሮፕላኑም ስላረፈ ጽሁፌንም ማቆም ስላለብኝ በዚሁ እየተሰናበትኩ እለያችሃለው ደህና ክረሙ።