ትክትክ/ጉንፋን

ሕብረት ወርሃዊ ጋዜጣ - ታደሰ ካህሳይ (http://www.ethio-calgary.ab.ca/)

ትክትክ/ጉንጋን ምንድነው?

ትክትክ (በተለምዶው አጠራር ጉንፋን) የሳምባና የአየር መተላለፊያ ቧንቧዎች ሕመም ሲሆን የሚተላለፈውም በዓይን በማይታይ የህዋስ አይነት (virus) ነው። ይህ በሽታ በተለያየ መልኩ በመላው ዓለም በየዓመቱ ይዘዋወራል። በሰሜን አሜሪካም በኅዳርና በሚያዝያ ወራቶች ውስጥ ብዙ ሰዎችን ያውካል። በተለይ ህጻናትንና እድሜያቸው ገፋ ያሉ አረጋውያንን ያጠቃል። ለዚህም ነው ሕብረት በኅዳር ወር ይህን ይዛ የቀረበችው።

የትክትክ ህዋስ ብዙውን ጊዜ በየአመቱ እየተቅያየረ ይመጣል። አብዛኛውን ወቅት ይህ በሽታ የነበረበት ሰው በመጠኑ ነው የሚጠቃው፤ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ይዞት ከነበረ ትልቅም ባይሆን ትንሽ ለተለወጠው ህዋስ መከላከያ አለውና ነው። ነገር ግን ይህ ህዋስ በየአምስት አመቱ አንድ ጊዜ ከፍ ያለ ለውጥ ያሳያል። ለዚህ አይነቱ ከፍተኛ ለውጥ ማንም መከላከያ ስለማይኖረው ህዋሱ (ቫይረስ) በመላው ዓለም በቀላሉ በቶሎ ይሰራጫል። እንደዚህ አይነቱ ዓለምቀፋዊ ወረርሽኝ በጣም አደገኛ የሆነ ሕመምና ሞትንም ሊያመጣ ይችላል።

የትክትክ በሽታ አደገኛነት የሚያጠያይቅ አይደለም - በተለይም የተፈጥሮ በሽታ መከላከያ ኃይላቸው በጣም ለቀነሰና ላነሰ ሰዎች። ትክትክ ለከፍተኛ አደጋ የሚጥለው የሳምባ ምችን ስለሚያስከትልም ነው። ለምሳሌ እንደ ህጻናት (ከሁለት ዓመት በታች ለሆኑ)፣ እድሜያቸው የገፋ አረጋውያንና የልብ፣ የሳንምባና የመሳሰሉ በሽታ ተጠቂዎች በተለየ ሁኔታ ይጎዳሉ። እስከ ሞት ሊያደርሳቸው ይችላል። ሌላው የሚያስከትለው ችግር በIኮኖሚም ላይ ነው - ብዙ ሰው ከስራ ቦታው ስልሚቀር የሰው አምራችነት በጣም ይቀንሳል፤ ት/ቤቶች ይዘጋሉ ወይም ብዙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከመከታተል ይቆጣባሉ። በመጨረሻም በጤና ተቋሞች ላይ ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል።

ትክትክ እንዴት ይተላለፋል?

የትክትክ/ጉንፋን ህዋስ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው የሚተላለፈው የታመመው ሰው ሲያስል፣ ሲያነጥስ ወይም ሲናገር ከመተንፈሻ አካሉ ወደአየር በሚረጩ ጥቃቅን ጠብታዎች (droplets) ነው። በአየር ላይ ያሉ ጥቃቅን ጠብታዎች (airborne droplets) ወደ ሰውነት ውስጥ የሚገቡት በአይን፣ በአፍንጫና አፍ ይሆናል። በምራቅ ውስጥ ያለው ህዋስ ከአንድ እስከ ሁለት ሜትር ርቀት በአየር ላይ ሊጓዝ ይችላል። ህዋሱ በደረቅ ቦታዎች ላይ ከአንድ እስከ ሁለት ቀኖች ሲቆይ በልብስ፣ በለስላሳ ወረቅት (tissue) እና በመደበኛው ወረቀት ላይ ደግሞ ከስምንት እስከ አስራ-ሁለት ስዓታት ይቆያል። በእጅ ላይ ከአምስት ደቂቃ ያላነሰ ይኖራል። በበሽታው የተያዘ ሰው ምልክቶቹን ማሳየት የሚጀምረው ከአንድ እስከ ሦስት ቀናት በበሽታው ከተለከፈ በኋላ ነው። ይህ በበሽታው የተያዘ ሰው በጣም አስተላላፊ የሚሆነው የመጀመሪያው የበሽታው ምልክቶች ከመታየታቸው አንድ ቀን በፊትና እስከ አምስት ቀናት ምልክቶቹ መታየት ከጀመሩ በኋላም ነው።

ምልክቶቹ ምን ይመስላሉ?

የትክትክ በሽታ ምልክቶች የሚከተሉትን ይመስላሉ፦

ያልታሰበና ያልተጠበቀ 38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ (100.4 ዲግሪ ፋራንሃይት) በላይ የሆነ ትኩሳት፤

ደረቅ ሳል፤

ውጋት የበዛበት የጠቅላላ ሰውነት ስሜትበተለይም ራስ፣ ወገብንና እግሮችን ሲያም፤

እጅግ በጣም የድካምና የስንፍና ስሜት ሲሰማ፣

የብርድ ስሜት፣ የአይን ውጋት፣ ምግብ የመብላት ፍላጎት ማጣት፣ የቆሰለ/የቀላ ጉሮሮ፣ የቀጠነ የአፍንጫ ፈሳሽና የተዘጋ አፍንጫንም ይጨምራል።

ከፍተኛው ትኩሳት ብዙውን ጊዜ ቶሎ ይወርዳል። ከዛም በሽተኛው ጤናማ ስሜቱን በሦስትና በአምስት ቀን ውስጥ ማግኘት ይጀምራል። የድካምና የመሳሉ ሁኔታ ግን ለብዙ ሳምንታት ሊቀጥል ይችላል። የትክትክ ምልክቶች ከተራው ጉንፋንና የሆድ ትክትክ (stomach flue) ተብለው ከሚታወቁት የተለዩ ናቸው።

ራሳችንን ክትክትክ እንዴት ምክላክል ይቻላል?

ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው የትክትክ ህዋስ ሁልጊዜ ስለሚቀያየር አዲስ የክትባት መድሃኒት በየዓመቱ ይዘጋጃል። አዲሱም መድሂኒት እስካሁን የታወቁትን ሦስቱን አይነት ህዋስ (virus) መከላከያ እንዲይዝ ሆኖ የተዘጋጀ ይሆናል። ይህም ማለት በየዓመቱ ክትባት (immunization) ያስፈልጋል ማለት ነው። ጥቅምትና ህዳር ጥሩ የክትባት ወራቶች ናቸው ምክንያቱም በነዚህ ወራቶች ነው የትክትክ በሽታ በብዛት የሚስራጨውና ነው። ክትባቱ ትክትክ በሽታን አያመጣም። ምክንያቱም ክትባቱ ውስጥ የሚገኘው ህዋስ የሞተ ስለሆነ ነው። ክትባቱ ለጤነኛ ሰዎች 70-90% በሽታውን የመከላከል ውጤት ያስገኛል። መከላከያውም ከስድስት ወር ላላነሰ ጊዜ ይሰራል። ክትባቱ ሌሎችን የመተንፈሻ በሽታዎች አይከላከልም/ አያገለግልም።

ክትባት መውሰድ የሌለባቸው ሰዎችም አሉ። እነሱም ከእንቁላል ጋር ችግር (allergic) ያለባቸው ሰዎች (ምክንያቱም መድሃኒቱ የሚሰራው ከእንቁላል ስለሆነ) ህጻናት (ከስድስት ወር በታች የሆኑ) ካሁን በፊት ክትባቱን ሲወስዱ ችግር (complication) ያጋጠማቸው ናቸው። ከፍተኛ ትኩሳት (fvr) ያለባቸው ሰዎች ትኩሳታቸው ሲያልፍ/ሲወርድ ክትባቱን መውስድ ይችላሉ።

ከክትባት ቀጥሎ ያለው ጥሩ የመከላከያ መንገድ እጅን በሚገባ መታጠብ ነው። እጅን መታጠብ የሚያስፈልገው፡

ምግብ ከመመገብ ወይም ከማዘጋጀት በፊት

ጥርስን ከማጽዳት/ ከመቦረሽ በፊት

የሰውነት ቁስልን ከማስታመም በፊት

የአይን መነጽርን (ኮንታክት ሌንስ) ከመቀየር በፊት

ትክትክ በሽታ ካለበት ሰው/አካባቢ ከቆዩ በኋላ:

መጸዳጃ ቤት ከደረሱ በኋላ

የራስን/የህጻናትን አፍንጫ ካጸዱ በኋላ

ካሳሉ/ካስነጥሱ በኋላ

ቆሻሻ ካጸዱ በኋላ

ሕጻናት መጫዎቻቸውን ከተጠቀሙ በኋላ እጃቸውን መታጠብ አለባቸው። በመደበኛ ሳሙናና በሚፈስ ለብ ያለ ውኃ እጅን መታጠብና የእጅ አልክሆል መጥረጊያም መጠቀም መልካም ነው። እጅን በሚገባ ለአስራአምስት ሰከንድ ያህል ከፈገፈጉትና ከታጠቡት የህዋሱን (የቫይረሱን) ቁጥር ይቀንሳል። የጤና ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ከዚህ በሽታም ሆነ ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ርቆ ጤነኛ ሕይወት ለመኖር ብዙ ውኃ መጠጣት፣ አለማጨስ፣ መደበኛና መጠነኛ የሰውነት ጥንካሬን ማዘወተር፣ ጭንቀትን መቀነስ፣ ተስፋ አለመቁረጥና ከማህብረሰብዎና አካባቢዎ ጋር ጤናማ ግንኙነት ማድረግ ጠቃሚ አስተዋጽዖ አላቸው። የበለጠ ለመረዳት www.healthlinkalberta.ca ይጐብኙ።