30 አመት በመድረክ ላይ ንዋይ ደበበ


ምንጭ: AddisZefen


የኢትዮጵያ ሙዚቃን እድገት በሦስት ደረጃ እከፍለዋለሁ :: የመጀመሪያው በእነአሰፋ አባተ ዘመን የነበረውና እነ ጥላሁን ገሠሠ ከሱዳን እና ከሕንድ ዜማዎችን እያመጡ ያሳደጉትን ሲሆን : ሁለተኛው ደግሞ እነ ነዋይ ደበበ ከሮሀ ባንድ ጋር በመሆን የሙዚቃውን ደርጃ ከፍ ያደረጉበት ነበር :: አሁን ሙዚቃ በአንድ ኪቦርድ ብቻ በመስስራት በኮምፒውተር ድምጽን አሳምሮ መምጣት በሆነበትና ካሴትና መድረክ በተለያዩበት ዘመን ሮሀ ባንድ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የሠራው ገድል የማይናቅ ነው ::

ሙዚቃን በሙሉ ባንድ በመስራት የመካከለኛውን ዘመን ሙዚቃ ጣሪያ ላይ የሰቀሉት ሮሀ ባንዶች ዛሬ በሞትና በሌሎችም የሕይወት ውጣ ውረዶች ባይነጣተሉ ምን ሊሰራ ይችል እንደነበር ሳስብ ያመኛል :: በእውነቱ ሮሀ ባንድ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አብዮተኛ ነበሩ ብል አላጋነንኩም ::

 

 

ሦሰተኛውና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ትንሣኤ የቴዲ አፍሮ እና የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ ) ነው :: በትክክለኛው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አብዮተኞች ተብለው በያሬድ ሙዚቃ አዋቂዎች የተመረጡት ሁለቱ ድምጻዊያን ሙዚቃን ዛሬ ለዚህ አብቅተዋታል :: በተለይ ቴዲ አፍሮ አብዛኞቹ ሙዚቃዎቹ ''ጠዋት ተመርቶ ከሰአት መርካቶ '' የሚለውን ብሂል ያስታውሰናል :: ይህን ለማረጋገጥም በሀይሌና በቀነኒሳ ዙሪያ የሰራውን ዘፈን እና እንዲሁም ለአዲሱ ሚሊኒየም ያቀርባቸውን ሥራዎች ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው ::
ቴዲ አፍሮ ለዛሬው የሙዚቃ መሠረትህ ማነው ? ሲባል ''ነዋይ ደበበ ነው '' ያለው :: ስለ ነዋይ ደበበ የሙዚቃ ሥራዎች : የግጥም ውበት እና አዘፋፈን ስልት አንስቶ የማይጠግበው ቴዲ ''በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የምሰጠው ነዋይ ደበበን ነው '' ይለናል :: በተለይ ቴዲ ገጣሚም : ዜማ ደራሲም ጥሩ አቀንቃኝም መሆኑ ከነዋይ ጋር ያመሳስለዋል ::
''
ነዋይ ደበበ የገበያ ዘፈኝ ነው '' ይለናል የአለም ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ሙኒር ኑርጀቦ :: 2 አመታት በፊት በኮፒራይት ሕግ መውጣት የተነሳ ኮፒ ካሴቶችን ያባዛል በሚል ታስሮ ከእስር የተፈታው ይህው የአለም ሙዚቃ ቤት ባለቤት ''ሕዝብ ምን ይፈልጋል ? የሚለውን የሚያውቅ ዘፋኝ ያስደስተኛል :: ነዋይ ሕዝብ የሚፈልገውን ነገር ያውቃል ::... ነዋይ ዛሬ ካሴት ቢያወጣ ሕዝቡ በአንድ ጊዜ ግጥምና ዜማውን መስማት ስለሚችልም ጭምር ገበያውን ይቆጣጠረዋል '' ይለናል ::
ዘንድሮ 30 አመት የሙዚቃ አገሎግሎት ዘመኑን የሚደፍነው ነዋይ ደበበ እንዴት ነበር ወደሙዚቃው አለም የገባው ? የሚለው የተለመደና አሰልቺ ሊሆን ስለሚችል በሙዚቃ አጀማመሩ ላይ ስላጋጠሙት አስልቺ አሳዛኝ ታሪኮች ልነሳ ::
ራስ ቲአትር በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር ሲቋቋም ለትያትር ቤቱ የተለያዩ አርቲስቶች በየሥራ ዘርፉ ይፈለጉ ነበርና በወቅቱ የወጣውን ማስታወቂያ በመመልከት ለፈተና ወደ አምባሳደር ትያትር ያመራል :: ይህ ወቅት ነበር ከነኤልያስ ተባበል : ሻምበል በላይነህ እና ከነጸሀይ ዮሀንስ ጋር ሊያስተዋውቀው የቻለው :: ነዋይ በወቅቱ ከወጣትነቱም ጋር በተያያዘ ድምጹ ቀጭን ቢሆንም ከፈታኞቹ መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ነዋይ ወደፊት ብዙ ሊሰራ ይችላል : ስለዚህም ራስ ቲያትርንም ለምንፈልገው ነገር ሊያግዘን ይችላል በሚል እንዲቀጠር አደረገው ::

 

ለነዋይ ደበበ ራስ ትያትር መግባት ምክንያት የሆነው ጋሽ ጥላሁን ገሠሠ

ወደ ሙዚቃው አለም የገባሁት እነጋሽ ጥላሁንን አይቼ ነው :: በጋሽ ጥላሁን እጅ ተፈትኜ የራስ ትያትር አባል ሆንኩ > የሚለው ነዋይ በራስ ቲያትር ጥሩ ጥሩ የሙዚቃ ልምዶችን እንዳገኘ አስታውቆ በወቅቱ በነበረው የግጥምና የዜማ መድረስ ችሎታው ለትያትር ቤቱ ዘፋኞች ግጥምና ዜማ ይሰጥ እንደነበር አስታውቋል ::

 

ከኤልያስ ተባበል : ጸሀይ ዮሀንስ : ሻምበል በላይነህ ጋር በመሆን ራስ ቲአትርን ገና በአዲስነቱ ሕዝብ በሕዝብ እንዲሆን ያደረገው ነዋይ በትያትር ቤቱ እየሠራ ሙዚቃ ለማውጣት ፈለገ ::

"ተስፋ አስቆራጭ ነገር ነበር :: ሙሉ ካሴት ሠርቼ ነበር :: ሙሉ በሙሉ ወቅቱን የጠበቀና ግጥሞቹም ዜማዎቹም ጥሩ ነበሩ :: የሙዚቃ አዋቂዎችም አይተውት ሥራዎቼን ወደዋቸው ነበር :: ይህ ከሆነ ለምን አስቀርጬ ለሕዝብ አላደርስም ብዬ በመጓጓት ሥራዎቼን ይዤ ወደ ሙዚቃ ቤቶች ይዤ ቀረብኩ :: በእውነቱ ከሙዚቃ ቤቶች አካባቢ ያገኘኍቸው ምላሾች ተስፋ አስቆራጭ እና በሙዚቃው አለም እንድቀጥል የማያደርጉ ናቸው ''” ይላል ::

ይቀጥልና ያጋጠሙትን ፈተናዎች ይተርካል ''.....የጥበብ ሥራ ላይ ስትሆን የሚያበረታታ ነገር ያስፈልግሀል :: ደካማ ነገህ ተነግሮህ ጠንካራ ነገሮችህ ሲነገሩህ ደስ ይላል :: ሆኖም ካሴቴን ለማሳተም በፈለግኩበት ጊዜ በሙዚቃ ቤቶች አካባቢ ያገኘሁዋቸው ምላሾች አንተ ድምጽህ ቀጭን ስለሆነ ለዘፈኝነት አትሆንም '' የሚሉ ነበሩ ይላል ::

በወቅቱ አብሮት የነበርው ጻሀዬ ዮሀንስ እድል አጋጥሞት የመጀመሪያ ካሴቱን ለሕዝብ ሲያደርስ የነዋይ ተሳትፎ የነበረበት ሲሆን በሙዚቃ አሳታሚዎች ይደርስበት የነበረውን ''አንተ ለሙዚቃ አትሆንም '' ትችት ተቋቁሞ ራሱን በማሻሻል ጥረቱን ቀጠለ ::

''የኢትዮጵያ አርስቲስት ኑሮ ከማንም የተደበቀ አይደለም :: በወቅቱ ካሴቱን በራሴ ላሳትም ብል ምንም አቅሙ አልነበረኝም :: አንዳንድ አሳታሚዎች እንደውም ግጥሙን እና ዜማውን ስጠንና ሌላ ዘፋኝ ይዝፈነው ሁሉ እያሉ ሞራሌን እስከመንካት ቢደርሱም በእግዚአብሄር ጥረት የታንጎ ሙዚቃ ቤት ባለቤት በመጨረሻም እስኪ ይሞከር ብለው ካሴቴን አሳተሙልኝ '' ይላል ::

ራስ ትያትር በተቀጠረ 3ኛው አመት ዝነኛው ድምጻዊ ጸሀዬ ዮሐንስ 'ተይ ሙኒት ' የተሰኘችውን አልበሙን አወጣ :: ከሕዝብ ጋር መልካም አቀባበልን ያደረገው ጸሐይ በአመቱ ፍንጭቷ የተሰኘውን ካሴት ደገመ ::

ነዋይ ደበበ ድምጽህ ለካሴት አይሆንም ተብሎ ሞራሉ ሳይነካ ጥረቱ ጥረቱ ቀጥሏል ''የኢትዮጵያ አርስቲስት ኑሮ ከማንም የተደበቀ አይደለም :: በወቅቱ ካሴቱን በራሴ ላሳትም ብል ምንም አቅሙ አልነበረኝም :: አንዳንድ አሳታሚዎች እንደውም ግጥሙን እና ዜማውን ስጠንና ሌላ ዘፋኝ ይዝፈነው ሁሉ እያሉ ሞራሌን እስከመንካት ቢደርሱም በእግዚአብሄር ጥረት የታንጎ ሙዚቃ ቤት ባለቤት በመጨረሻም እስኪ ይሞከር ብለው ካሴቴን አሳተሙልኝ '' ይላል ::

ነዋይ በወቅቱ ከጎኑ የነበሩትን ታዋቂ የሙዚቃ ባለሙያ ጋሼ ተስፋዬ ለማን እጅጉን ያመሰግናል :: የወቅቱ የራስ ትያትር ስራ አስኪያጅ የነበሩትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን መስርተው የነበሩት እኚሁ አርቲስት በነዋይ ደበበ የዛሬው የሙዚቃ ስኬቱ ላይ ትልቅ ድርሻ አላቸው :: ለዚህም ነው አርቲስት ተስፋዬ ለማን ''ጋሼ '' ብሎ የሚጠራቸው ::

''ጋሼ ተሰፋዬ ብዛት ያላቸው የሙዚቃ ጥበቦችን አስተምረውኛል :: በራስ ትያትር ውስጥም ሆነ ራሳቸው በመሰረቱት ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ትምህርቶችን እንድቀስም አድርገውኛል '' ሲል ምስክሩን ይሰጣል ::

ነዋይ እስኪ ሞክር ተብሎ የመጀምሪያ ካሴቱን በታንጎ ሙዚቃ ቤት አማካኝነት አወጣ :: በአሳታሚዎች ድምጽህ ቀጭን ነው ተብሎ ይፈራ የነበረው ነዋይ : ለዘፋኝነት ሳይሆን ለግጥምና ዜማ ደራሲነት ነው የምትሆነው የተባለው ነዋይ : አሳታሚዎች ፊት የነሱት ነዋይ ማንነቱን አሳየ :: በመጀመሪያ ሥራውም ከሕዝብ ጋር ለመተዋወቅ በቃ ::

በወቅቱ ነዋይ መሀል ፒያሳ ወደ ሚገኘው ታንጎ ሙዚቃ ቤት ይመላለስ ነበር :: የሚመላለሰው እንደሚባለው የመጀምሪያውን ካሴቱን ሲያወጣ በከቨር ሽያጭ በመሆኑ በየቀኑ የተሸጡትን ኦሪጂናል ከቨሮች ለመከታተልም : እንዲሁም ስለቀጣይ ስራዎችም ለመነጋገር ሲሆን በመጀምሪያው ካሴቱ የተማረኩት የታንጎ ሙዚቃ ቤት ሰዎች ሁለተኛውን ካሴት እንዲደግም አደረጉት ::

ሁለተኛው የነዋይ ደበበ ካሴት በሕዝብ ዘንድ እጅጉን የተወደደ ከመሆኑም በተጨማሪ የተለያዩ አድናቆቶችን ያጎርፉለት ጀመር ::

በወቅቱ ከነበሩት የጥበብ ሰዎች መካከል የራስ ቲአትር የኪነጥበባት ክፍል ሀላፊ የነበረችው የቀድሞዋ የጸሐዬ ዮሀንስ ባለቤት አዳነች ወልደገብርኤል ለነዋይ ደበበ ቅርብ ነበረች ::

 

''የነዋይ ውስጡ ያለው ጥበብ ይገርመኝ ነበር :: በየቀኑ ጠዋት ወደ ትያትር ቤታችን የሙዚቃ ክፍል ይዞ የሚመጣው አዳዲስ ነገሮችን ነበር :: በተለይ ግጥምና ዜማዎቹ ከእርሱ የሚወጡ አይመስሉም ነበር '' ስትል አድናቆቷን ትገልጻለች ::

አርቲስት አዳነች ወልደገብርኤል የጸሀዬ ዮሀንስ የቀድሞ ባለቤቱ ስትሆን ከድምጻዊውም ኢየሩሳሌም የምትባል ልጅ አለቻት :: ከጸሐዬ ጋር ከተለያዩ በኍላም አርቲስቷ በጸሐዮ ዮሐንስ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ''የእሳት እራት '' የተሰኘ ፊልም መነሻ ሀሳብ ሰጪ በመሆን ማሰራቷ ይታወሳል :: ይህ ፊልም 1992 አካባቢ የወጣ ሲሆን ጸሐዬ ''የእኔ ታሪክ አይደለም : እኔን ለመጉዳት ሆን ብላ ያሰራችውና የተጋነነ ፊልም ነው '' ሲል አዳነችን መተቸቱን አስታውሳለሁ ::

 

ፊልሙን ከሰሩት መካከል ታዋቂዋ አርቲስት መሰረት መብራቴ (ጉዲፈቻ ፊልም ላይ ያለችው ቆንጆ ) ''ፊልሙን ሥሰራው የጸሐዬ ዮሐንስ ታሪክ መሆኑ እየተነገረኝ ስለሆን አልቅሻለሁ '' ብላ ራሴው በምሳተፍበት ጋዜጣ ላይ መግለጫ መስጠቷም ይታወሳል :: ይህ ፊልም ከወጣ በኍላ ጸሀዬ ዮሀንስ ''ተበድዬስ ይቅርታ አልልም '' የሚለውን ተወዳጅ ዘፈኑን በቴሌቭዥን አስቀርጾ ለሕዝብ ወዲያው ማድረሱን ተከትሎም ለአዳነች የተሰጠ ምላሽ ነው ተብሎም ተተችቶ ነበር ::

ወደ ነዋይ ታሪክ ስንመለስ 2 ካሴቱን ከታንጎ ሙዚቃ ቤት አውጥቶ ከስኬት እና ከገንዘብ ጋር ከሙዚቃ ቤቱ ይዞ የሄደው የአሁኗን የልጆቹን እናት ባለቤቱን ጭምር ነበር :: ብዙ የአርቲስቶቻችን የፍቅር ሕይወት ግልጽ ስለማይሆን እንጂ በዚህ ዙሪያ ላይ ብዙ ማለት ይቻል ነበር :: ሆኖም የነዋይ ባለቤት ሙስሊም ከመሆኗ አንጻር ማስታወሻ የሚባል የኪነጥበብ መጽሔት ''ነዋይ ባለቤትህ ሙስሊም ናት :: አንተ ደግሞ ክርስቲያን ናት :: አስባችሁበታል ወይ ? የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነዋይ ''አዎ :: ባለቤቴ ወላሂ ስትለኝ አምናታለሁ እኔ ደግሞ ኪዳነምህረትን ስላት ታምነኛለች '' ያለው መልሱ እስከአሁን ከአእምሮዬ አይጠፋም ::

ዘፈኖቼ ሁሉም የየዘመኑ ውለታና ትዝታ አለው :: ሁሉም የየዘመኑና አስተዋጽኦ ሁሉ አለውና ይህኛው ከዚኛው ለማለት ባልደፍርም ሁል ጊዜ እኔ መጀመርያ ስራ የጀመርኩበት ሥራ ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀኝ ነውና እሸት በላሁኝ”: “የጥቅምት አበባ ከሌሎቹ ለየት ይልብኛል :: ከዚያ ውጭ ያሉት በሂደት ላይ ስለሆነ አንዱ ከአንዱ ለመለየት ያስቸግራል::” የሚለው ነዋይ ደበበ 30 አመት የሙዚቃው አለም ቆይታው ክፉንም ደጉንም አይቶአል

የነዋይ ደበበ አድናቂ ነኝ :: ከዘፋኝነቱ ውጭ ባህሪው እንዲሁም የግጥምና ዜማ ደራሲነቱን አደንቃለሁ :: ብዙ ጊዜም መድረክ ላይ የእርሱን ዘፈኖች እዘፍናልሁ :: ባጠቃላይ አፌን የፈታሁት በነዋይ ደበብ ሥራዎች ነው ማለት እችላለሁ

- ቴዲ አፍሮ

1994 . ከአሌክስ ጋር በጋራ በሰራነው ካሴት ላይ ስለ ሀመር የዘፈንኩበት ዘፈን አለ :: ኢቫንጋንዲ የሚለው :: ይህን ስራ ከወደዱት አርቲስቶች መካከል አድናቆቱን የሰጠኝ ነዋይ ደበበ ብቻ ነው :: ነዋይ ስለሀመር እኔ ሳልዘፍን አንተ ስለዘፈንከው አመሰግናለሁ ብሎ አብረታቶኛል :: በተለይ ለወጣት ድምጻዊያን ሞዴል ነው ::”

ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ

በርከት ከት ያሉ ወጣት ድምጻዊያን ስለነዋይ የሚናገሩት አንድ አይነት ነግሮችን ነው :: ከአሁኑ ዘመን ወጣት ድምጻዊያን መካከል አብዛኞቹ አርአያ አድርገው የሚጠቅሱት ነዋይን ነው :: ሙዚቃ ቤቶችም ቢሆኑ የነዋይን ካሴት በጉጉት ነው የሚጠብቁት :: 1994/5 ነዋይ ''ደሀ ናት '' የሚለውን ካሴቱን ሲያወጣ በኢትዮጵያ ውስጥ የኮፒ ራይት ህግ ባለመኖሩ አንዱ በሰራው ያልሰራው የሚጠቀምበት ጊዜ ነበር :: ያን ጊዜ አሳታሚ ሙዚቃ ቤቶች በአንድ በኩል ኦሪጅናል በሌላ በኩል ቅጂ ካሴት የሚሸጡበት ወቅት በመሆኑ ለነዋይ ደበበ ካሴት ተገቢውን ክፍያ ከፍሎ የሚያከፋፍል ሙዚቃ ቤት ጠፋ :: ታዋቂው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት በኮፒ ካሴት ሽያጭ የተነሳ ዋናውን ሳልመልስ እከስራለሁ በሚል ራሱ ካሴቱን አላከፋፍል አሉ :: የዛን ጊዜ ነበር አዳነች /ገብሬል ለነዋይ ደበበ ትልቅ ሥራ የሰራችው :: ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምታውቁት ኮፒ ካሴት 7 ብር እና 6 ብር ነው የሚሸጠው::: ኦርጂናሉ ደግሞ 13 ብር :: አዳነች ከነዋይ ጋር በመመካከር የኦርጂናሉን ካሴት ዋጋ ወደ 10 ብር ቀንሳ እንዲሸጥ አደረገች :: 3 ብር ብሎ ቅጂ ካሴት የሚገዛ የለምና ካሴቱ እንደጉድ ተሸጠ :: የነዋይን ይህን ካሴት ተከትሎ በርካታ አርቲስቶች የካሴት መሸጫ ዋጋቸውን ወደ 10 ብር ዝቅ አድርገውት እንደነበር አስታውሳለሁ :: ጥሩ ፈጠራ ነበር። ሰላም ቆዩኝ።


Write a comment

Comments: 0